እንቅልፍና እርግዝና

በእርግዝና ወቅት የሚኖረው የአካላዊ ምቾት ማጣት እና የሆርሞን(እድገንጥር) ለውጥ የአንዲት እርጉዝ ሴት የእንቅልፍ ጥራት ላይ ተፅኖ ያሳድራል፡፡ እያንዳንዳቸው የእርግዝና ሦስት ሦስት ወራት ልዩ የሆኑ የእንቅልፍ ተግዳሮቶችን ያመጣሉ፡፡ የብሔራዊ እንቅልፍ ድርጅት እንደሚለው የሚከተሉት በያንዳንዱ ሦስት ወር በብዛት የሚፈጠሩ የእንቅልፍ ለውጦች ናቸው፡

እንቅልፍ በመጀመሪያ ውሦስትወር

  • ሽንት ቶሎ ቶሎ ስለሚመጣ ወደ መፀዳጃ ቤት ለመሄድ ከእንቅልፍ መንቃት
  • ከእርግዝና ጋር በተያያዙ አካላዊና ስሜታዊ ጫና ምክንያት የተረበሸ እንቅልፍ
  • ቀን ላይ እንቅልፍ እንቅልፍ ማለት

እንቅልፍ በሁለተኛው ሦስት ወር

ለብዙ ሴቶች ሁለተኛው ሦስት ወር የተሻለ ነው፣ ምክንያቱም ፅንሱ ከፍ በማለት የሽንት ፊኛ ላይ አሳድሮት የነበረውን ጫና ስለሚቀንስ ለሊት ለሽንት መንቃትን ይቀንሳል፡፡ አሁንም ቢሆን እያደገ ባለው ፅንስ እና ስሜታዊ ጫና ምክንያት የእንቅልፍ ጥራቱ ላይሻሻል ይችላል፡፡

እንቅልፍ በሦስተኛው(የመጨረሻው) ሦስት ወር

ቀጥሎ በተዘረዘሩት ምክንያቶች ብዙ ከእንቅልፍ ጋር የተያያዙ ችግሮች የሚያጋጥሙሽ በዚህ ወቅት ነው

  • እያደገ ባለው ሆድሽ ምክንያት ምቾት ማጣት
  • የጨጓራ ማቃጣል፣ የእግር መሸማቀቅ፣ እና የአፍንጫ መታፈን
  • የልጁ ቦታ መለዋወጥ የሽንት ፊኛ ላይ ጫና ስለሚያሳድር፣ ለሊት ሽንት ቶሎ ቶሎ መምጣት እንደገና ይጀምራል

በእርግዝና ጊዜ ጥሩ እንቅልፍ ለመተኛት ጠቃሚ መረጃዎች

ከሚቀጥሉት መረጃዎች መካከል አንዱ ወይም ከዛበላይ በእርግዝና ጊዜ ጥሩ እንቅልፍ እንድትተኚ ሊረዳሽ ይችላል፡፡ ነገር ግን የእንቅልፍ ችግርሽ ከባድ ከሆነ ሐኪም ማማከር አለብሽ

  • ተጨማሪ ትራሶች፡ ትራስ ሆድሽን እና ጀርባሽን ለመደገፍ ልትጠቀሚበት ትችያለሽ፡፡ ትራስ በእግሮችሽ መሐል ማድረግ ወገብሽን ለመደገፍና በጎን መተኛትን ያቀልልሻል፡፡
  • አመጋገብ፡ ለበ ያለ አንድ ብርጭቆ ወተት መጠጣት እንቅልፍሽን ሊያመጣው ይችላል፡፡ እንደ ዳቦና ብስኩት ያሉ በካርቦ ሃይድሬት የበለፀጉ ምግቦችም ለእንቅልፍን ጥሩ ናቸው፡፡ በተጨማሪም በፕሮቲን የበለፀጉ መቆያ ምግቦች የደም የስኳር መጠንን በመጨመር ቅዠቶችን፣ እራስ ምታትንና ድንገተኛ ላብ ላብ የማለት ወይም የሙቀት ስሜትንይከላከላሉ፡፡
  • ዘና የማለት ዘዴዎች፡ ዘና ማለት አእምሮሽን ረጋ እና ጡንጫሽን ለማፍታታት ይረዳሻል፡፡ እነዚህ ዘዴዎች ጡንቻዎችሽን ማሳሳብ፣ ዮጋ፣ ማሳጅ፣ ጥልቅ አተነፋፈስ እና ለብ ባለ ውሃ መታጠብ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
  • በሐኪም ትዛዝና ካለትዛዝ የሚሸጡ መድሃኒቶች፡ ከተቻለ ሁሉም መድሃኒቶች በእርግዝና ወቅት ባይወሰዱ ይመረጣል፡፡ አንዳንድ መድሃኒቶች የፅንሱን እድገት ሊጎዱት ይችላሉ፡፡ ነገር ግን በእርግዝና ወቅት የተሻለ እንቅልፍ ለመተኛት የሚረዱ ጉዳት የሌላላቸው ተብለው የሚታመኑ መድሃኒቶች አሉ፡፡ ሁል ጊዜ ማንኛውንም አይነት መድሃኒት ከመውሰድሽ በፊት ሐኪምሽን ማማከርሽን አትርሺ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *