በዚህ ሣምንትሁሉም የሰውነት ክፍሎቹ የውጭውንአለምለመቀላቀል ዝግጁሆነው ተሟልተዋል። ጽንስበ ማህፀን ውስጥ የተለያዩ አቀማመጦች ይኖሩታል፡፡ ማህፀን ውስጥ በቂቦታስለሚኖርጽንሱእንደፈለገይገለባበጣል፤ በየጊዜው በመገለባበጥ የተለያዩ አቀማመጦችን ይይዛል፡፡
በፊት በፊት ፅንስ 37 እና 38ተኛ ሳምንት ላይ ሲደርስ ሙሉ የእርግዝና ጊዜውን እንደጨረሰ ይታመን ነበር፡፡ ነገር ግን እንደ የአሜሪካ ማህፀንና ፅንስ ምክርቤት ግኝት በ39ነኛ እና 40ኛ ሳምንት የሚወለዱ ልጆች በ37 እና 38ተኛ ሳምንት ከሚወለዱት ይልቅ የተሻለ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ፡፡ በተጨማሪም ጥናቱ ከ39ነኛ ሳምንት በፊት የፅንስ መጨናገፍ እድሉም ከፍ ያለ እንደሆነ አሳይቷል፡፡ በነዚህ ምክንያቶች የተነሳ አንድ ፅንስ ሙሉ ጊዜውን ጨረሰ የሚባለው 39ኛ ሳምንት ላይ ሲሆን ነው፡፡
የልጁ እድገት
የአንጎል እድገት
የአንጎል እና የስረዓተ ነርቭ እድገት በማህፀን ውስጥ ይቀጥላል፡፡ በዚህ ሰዓት አንጎል የደም ዝውውርን ፣አተነፋፈስን እና የምግብ መፈጨትን የመሰሉ የአካል ስራዎችን መቆጣጠር ይጀምራል፡፡
ውስጣዊ የሰውነት ክፍሎች እድገት
አሁን ሁለም የሰውነት ክፍሎች ልጅሽ ሲወለድ የሚጠበቅባቸውን ስራ ለመከወን ሙሉ እድገታቸው ላይ ደርሰዋል፡፡ ብቸኛውና ትንሽ የመጨረሻ መስተካከል የሚቀረው ሳንባ ብቻ ነው፡ ሳንባ በማህፀን ውስጥ አየር ስለሌ ስራውን መለማመድ አይችልም፣ ስራውን የሚጀምረው ልክ ልጁ ሲወለድ ነው፣ ፡፡ በዚህን ጊዜ ሳንባ ብዙ መጠን ያለው ገፀ አግባሪ(ሰርፋክታንት) ያመርታል፣ ይህ ኬሚካል ልጁ መተንፈስ ሲጀምር የአየር ከረጢቶች እርስ በርሳቸው እንዳይጣበቁ ያደርጋቸዋል፡፡
ስርዓት-ልመት አስቀድሞ ስራውን ጀምሯል፣ የልጅሽን የመጀመሪያ የአንጀት እንቅስቃሴ ውጤት የሚሆነውን አረንጓዴ እና የሚያጣብቀውን ቁጣጥ እያመረተ ነው፡፡ ቁጣጡ ከሽርት ውሃው ጋር አብሮ የሚዋጠውን ላኑጎ ፀጉር የሚባለውን ፅንሱ በመጀመሪ ጊዜ የሚያበቅለውን ፀጉር እና በእርግዝና የመጨረሻ ደረጃ ላይ በፅንሱ የሚገፈፈውን ሲወለድ በቆዳው ላይ የሚታየውን ነጭ ሽፋን የያዘ ነው፡፡
ውጫዊ ገፅታ
ልጅሽ ከማህፀን ሲወጣ የሰውነት ሙቀቱን ለመቆጣጠር የሚረዳው የቆዳ ስብ ገና እያደገ ነው፡፡ የቆዳ ቀለሙም ወደ ትክክለኛ ቀለሙ እየቀረበ ነው፡፡
ልጅሽ ምን ያክል ትልቅ ነው?
በ38ተኛው ሳምንት ልጅሽ ቁመቱ 49.78 ሴ.ሜ፣ ክብደቱ 3.17 ኪ.ግ አካባቢ ይሆናል፡፡ የስብ ክምችቱ እየጨመረ ቢሆንም ወደ መወለጃው መጠን እየተቃረበ ሲመጣ ክብደቱ መጨመሩ ይቀንሳል፡፡
የልጁ አቀማመጥ
ልጅሽ በዚህ ሳምንት ለመወለድ በሚያመች አቀማመጥ ላይ ይሆናል፣ ጭንቅላቱ ወርዶ ዳሌ አጥንት ውስጥ ገብቶም ሊሆን ይችላል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ግን ልጁ ሳይገለበጥ ሊቀር ይችላል፣ በመጨረሻው ሦስት ወር መጨረሻ ደረጃ ላይ እግሩ ወደታች እንደሆነ ሊቀር ይችላል፡፡ ይህን ለማስተካከል ሐኪምሽ ሆድሽ ላይ አንዳንድ ቦታዎችን ከውጪ ጫን በማለት ልጁን የመገልበጥ ሃሳብን ሊያቀርብ ይችላል፡፡ ይህ እርምጃ የፅንሱ ክብደት፣ የእናትየው እድሜ እና የፅንሱ አቀማመጥ ላይ ተመርኩዞ 50% የመሳካት እድል አለው፡፡ እግራቸው ወደታች ሆነው የሚቀሩ ልጆች የሚወለዱት በቀዶ ጥገና ነው፡፡
በሰውነትሽ ላይ የሚፈጠሩ ለውጦች
አዎንታዊው ነገር ልጅሽ ወደታች ዝቅ ስለሚል የምግብ አለመፈጨት የጨጓራ ማቃጠል ስሜቶች ይጠፋሉ፣ ሳንባሽም ለመለጠጥ ቦታ ስለሚያገኝ የደረት ህመም እና የትንፋሽ ማጠር ስሜቶችም መፍትሄ ያገኛሉ፡፡ ነገር ግን በተመሳሳይ ሰዓት ፅንሱ የሽንት ፊኛ ላይ የሚፈጥርው ጫና በዕጥፍ ያድጋል፣ማለትም ወደ መፀዳጃ ቤት መሄድን ይጨምረዋል እንደውም አንዳንድ ጊዜ በማስነጠስ እና በሳቅ ጊዜ ሽንት ሊያመልጥ ይችላል:: የሰውነት መጨመርሽ በ37ተኛው እና 38ተኛው ሳምንት ላይ እየቀነሰ ይመጣል፡፡ አንዳንድ ሴቶች ጡታቸው ወፍራም ቢጫ ነገር ማመንጨት ይጀምራል፣ እንገር ይባላል፡፡ አዲስ የተወለደውን ህፃን ከበሽታ መከላከል እንዲችል የሚጠቅሙትን ንጥረ ነገሮች ይይዛል፡፡
ሰውነትሽም ለመውለድ ይዘጋጃል፣ ልጅሽ በማህፀን አንገት ማለፍ እንዲችል ማህፀንሽ መከፈትና መሳሳት ይጀምራል፡፡
የመንታ እርግዝና 38ተኛ ሳምንት
ብዙ መንታ እርግዝናዎች 37ተኛ ሳምንት ላይ ስለሚወለዱ 38ተኛ ሳምንት ላይ የሚደርሱት ጥቂት ናቸው፡፡ ስለዚህ ምጥሽ በማንኛውም ሰዓት ሊመጣ ስለሚችል ዝግጁ መሆን አለብሽ፡፡ ሐኪሞች ሆስፒታል መውለድን ይመክራሉ ምክንያቱም ከጊዜያቸው ቀድመው የሚወለዱት ህፃናት ወድያውኑ ልዩ እንክብካቤ ሊያስፈልጋቸው ስለሚችል ነው፡፡ መንታ እርግዝናዎች ብዙ ጊዜ የተወሳሰቡ ናቸው፣ ቢሆንም 38ተኛ ሳምንት ላይ የተወለዱ ህፃናት ለአንድ ሳምንት በጨቅላ ህፃናት ልዩ ማቆያ ውስጥ ከቆዩ ጥሩ ሁኔታ ላይ ይሆናሉ፡፡
በዚህ ሳመንት የሚደረጉ ምርመራዎች
በ38ተኛው ሳምንት ላይ የሚደረገው ቅድመ ወሊድ ምርመራ ልጁ ከመወለዱ በፊት የምታደርጊው የመጨረሻ ምርመራሽ ነው የሚሆነው ፣ እርግዝናሽ ከ 40 ሳምንት በላይ ካልቆየ በስተቀር ፡፡ በዚህ ጊዜ በተቻለ መጠን ስለአወላለድሽ እና ስለምጥ ሐኪምሽን በደንብ ማማከር አለብሽ፡፡
ሐኪምሽ የልጅሽን የማህፀን ውስጥ አቀማመጡን ለማወቅ ወይም አቀማመጡን ለመቀየር ከውጪ ጫና ማድረግ ካላስፈለገ በስተቀር አልትራሳውንድ መነሳት አያስፈልግሽም፡፡
ሐኪምሽ ማህፀንሽ መከፈት መጀመሩን ለማወቅ ተጨማሪ አካላዊ ምርመራዎችን ያደርግልሻል፡፡ የማህፀን በርሽ 10ሴ.ሜ ሲከፈትና 100% ሲሳሳ ለመውለድ ዝግጁ ትሆኛለሽ፡፡ መከፈቱና መሳሳቱ የመጀመሪያ እርግዝና ጊዜ የሚጀምረው ምጥ ከመጀመሩ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ሲሆን፣ ሁለተኛ እርግዝና እና ከዛ በኃላ ደግሞ ወዲያወ ምጥ ሊጀምር ሲል ነው፡፡
የ38ተኛው ሳምንት እርግዝና ምልክቶች
- የማህፀን መኮማተር ወይም ጥንክር የማለት ስሜት
- የዳሌ አጥንት ህመም
- ከእምብርት በታች የሆድ ክፍል ላይ ወይም ብልት አካባቢ የሚሰማ ውጋት
- የእግር መሸማቀቅ
- የጭራ አንጓ ህመም
- እብጠት በተለይ የእጅና የእግር
- የመገጣጠሚያ(የጉልበት፣ የዳሌ እና መንገጭላ)፣ የጭን እና የጀርባ ህመም
- ማሳከክ በተለይ በተወጠረው ሆድ አካባቢ እና ጡት አካባቢ
- የቆዳ ሸንተረር
- ራስ ምታት፣ ድንገተኛ የሙቀት(የማቃጠል)ስሜት፣ የጉሮሮ ህመም
- የደም ስር እብጠት፣ ኪንታሮት
- የሆድ ድርቀት ወይም ተቅማጥ
- እንቅልፍ ማጣት እና በእረፍት ጊዜ የሚያም የእግር ህመም
- ድብርት እና ቶሎ ቶሎ የስሜት መለዋወጥ
- የእጅ እና የእግር መቆጥቆጥና መደንዘዝ
የ38ተኛው ሳምንት ምጥ ምልክት
ምጥ በ38 እና 42ተኛ ሳምንት መኃል በየትኛውም ጊዜ ሊጀምር ይችላል፡፡ ስለዚህ የሚቀጥሉትን የምጥ ስሜቶች መከታተል ይመከራል
- በአንድ ሰዓት ውስጥ 5 ወይም ከዛ በላይ የሆነ የማህፀን መኮማተር(ቁርጠት)
- የወር አበባ አይነት ቁርጠት
- ከእምብርት በታች የሆድ ክፍል ላይ እና ዳሌ አካባቢ የግፊት ስሜት
- መድማት
- ከማህፀን የሚወጣ ፈሳሽ መብዛት
- ቀጣይነት ያለው ወይም መጣ ሄድ የሚል የሚርገበገብ የጀርባ ህመም
- ብዙ የጠራ ውሃ መሰል ፈሳሽ ወይም ሽርት ውሃ መንጠባጠብ
- ጉንፋን መሰል ስሜት(ማቅለሽለሽ፣ ማስመለስ እና ማስቀመጥ)
- ቡናማ፣ ሮዝማ ወይም ደም ያለው ንፍጥ መሰል ፈሳሽ መታየት
መቼ ነው ወደ ሐኪም መሄድ ያለብሽ
- ከላይ የተጠቀሱት የምጥ ስሜቶች ካሉሽ
- የልጅሽ እንቅስቃሴ መቀነስ ሲሰማሽ
- ሽንትሽን ስትሸኚ የማቃጠል ስሜት፣ ሽታ ቢኖረውም ባይኖረውም ደመናማ ወይም ጠቆር ያለ ሽንት ፣ የታችኛው ወገብ እና/ወይም ከእምብርት በታች ሆድ ህመም(ኩላሊት አካባቢ)፣ ወፍራም ነጭ ወይም አረንጓዴኣማ ቢጫ ዝልግልግ ፈሳሽ፣ ትኩሳት፣ ማቅለሽለሽ፣ በግብረ ሥጋ ግንኙነት ጊዜ የህመም ስሜት (የኩላሊት/የፈንገስ ወይም የሽንት ቱቦ ኢንፌክሽንን ሊያመለክት ይችላል)
- ከባድ ድካም እና እራስ ማዞር ከድንገተኛ የእይታ ብዥ ማለት እና የማያቋርጥ እራስምታት፣ ድንገተኛ የፊትና የእጅ ማበጥ፣ ከእምብርት በላይ የሆድ ህመም እና አየር ማጠር(የደም ግፊት መጨመርንና በእርግዝና ጊዜ የሚከሰት ደም ግፊትን ሊያመለክት ይችላል)
- በድካም የታጀበ ከመጠን በላይ የሆነ ውሃ ጥምና የአፍ መድረቅ፣ ማዞር፣ ከበፊቱ በበለጠ ሽንት የመምጣጥ ስሜት፣ ትንፋሽ ማጠር፣ በተደጋጋሚ የሚከሰት የሽንት ቱቦ ኢንፌክሽን እና በሽንት ውስጥ ኬቶን መገኘት(በርግዝና የሚመጣ የስኳር ህመምን ያመለክታል)
- በአንድ በኩል ብቻ ማበጥ ወይም አንድ እጅ፣ እግር ወይም ቁርጭምጭሚት ብቻ ማበጥ(የደም መርጋት ችግርን ሊየመለክት ይችላል)
- በመደበኛ ህክምና የማይቆም ኃይለኛ የውስጥ እጅ እና የውስጥ እግር ማሳከክ ( በደም ውስጥ የሃሞት አሲድ መጠራቀም ወይም የጉበት ህመምን ሊየመለክት ይችላል)
ለጤናማ እርግዝና እና ጤነኛ ልጅ ጠቃሚ መረጃዎች
- ቅመም የበዛባቸው ምግቦችን መተው፣ የምግብ አለመፈጨትን እና የጨጓራ ማቃጠልን በመቀነስ ማታ ላይ ጥሩ እንቅልፍ እንድትተኚ ይረዳሻል፡፡
- ቀለል ያሉ ምግቦችን እንደ ፓስታ እና ከጥራጥሬ የተሰሩ ብስኩቶችን መመገብ የማቅለሽለሽ ስሜትን ያስታግሳል፡፡
- ቀለል ያሉ እንደ ዋና የእግር ጉዞ የመሳሰሉ የአካል እንቅስቃሴዎችን ማድረግ በመጨረሻ የእርግዝና ሦስት ወራት አማካኝነት የሚመጣውን የጀርባ እና የሆድ ህመምን፣ የእግር መሸማቀቅን እና በዳሌ አካባቢ ምቾት ማጣትን ይቀንሳል
- እንደ የጉሎ ዘይት ባሉ ተፈጥሮአዊ በሆኑ መንገዶች ምጥሽን ለማምጣት ወይም ለማፋጠን ካሰብሽ ሐኪምሽን አማክሪ፡፡