34ኛዉ ሳምንት

በ34ተኛዉ  ሳምንት  በአማካይ  የልጅሽ  ክብደት 2.3  ኪሎግራም  እንዲሁም  ርዝመቱ 45 ሴንቲሜትር  ያህል ይሆናል፡፡45ሴንቲሜትር  ከእግር  ጥፍሩ  እስከ  ራሱ  ያለዉ ቁመት ነዉ፡፡  እንግዲህ  ለመዉለድ  ከሁለት  ወር ያነሰ ጊዜ ቀርቶ ሻል፡፡ ልጅሽ በሆድሽ ዉስጥ መገላበጡን መንቀሳቀሱን  ቀጥሏል፡፡  ክብደቱ  በሄደ ቁጥር የልጅሽ እንቅስቃሴና እርግጫዉ መጠኑ እየጨመረ ይሄዳል፡፡  የእንቅስ ቃሴዉ ኡደት ወይንም  ድግግሞሹ (ፍሪኩዌንሲዉ) ተመሳሳይነት  አለው፡፡  የልጅሽ  የመስማት ችሎታዉ አድጓል፤ በተለይ  ጮክ ያሉ ድምፆችን  የበለጠ  ይሰማቸዋል፡፡  የልጅሽ  የነርቭ ስርዓት በማደግ ላይ ነዉ፡፡ ሳንባዉም እያደገ ነዉ፡፡ በአጠቃላይ ልጅሽ በዚህ ሳምንት ከሆድሽ ዉጭ ወይም ከማህፀንሽ ዉጭ የመኖር አቅም አለዉ ፡፡ ድንገተኛ ሊወለድ ይችላል፡፡

 

ምናልባት  ስለምጥ ከወዲሁ መጨነቅ  ከጀመርሽ፤  በ34ኛዉ እና በ37ኛዉ  ሳምንታት መካከል የሚወለዱ ልጆች ምንም የጤና እክል አያጋጥማቸዉም፡፡ ሆኖም ከተወለዱ ቡኋላ ማሞቂያ ክፍል ለተወሰነ ጊዜ መቆየት ግድ ሊሆንባቸዉ ይችላል፡፡ ሌላ ተጨማሪ የጤና ችግር ከሌለባቸዉ በስተቀር 9 ወር ወይም 40 ሳምንት ጠብቆ ከሚወለዱ ልጆች እኩል ጤንነት ይኖራቸዋል፡፡

የምትወልጂዉ ልጅ ወንድ ከሆነ የዘር ፍሬዉ በዚህ ሳምንት ወደ ሽፋሽፍት ይወርዳል፡፡ 95በመቶ ወንድ ልጆች በዚህ ሳምንትናበሚቀጥሉት ሳምንታት የዘር ፍሬያቸው ወደ ሽፋሽፍት የሚወርድ ሲሆን፤ ቀሪዎቹ 5 በመቶ ደግሞ ከተወለዱ ቡኋላ ባሉት ሳምንታት ዉስጥ አልያም በመጀመሪያዉ አመት ዉስጥ ይጠናቀቃል፡፡

በ34ኛዉ እና በ36ኛዉ ሳምንታት መካከል የእንሽርት ውሀ (የአሚኖቲክ ፍሉድ) ከፍተኛ መጠን የሚደርስበት ነዉ፡፡ በ37ኛዉ ሳምንት ደግሞ የአአሚኖቲክ ፍሉድ መጠኑ መቀነስ ይጀምራል፡፡  የእንሽርት ውሃውን (የአሚኖቲክ ፍሉዱን) ሰዉነትሽ መልሶ ይመጠዋል፤ ይህም ለልጅሽ ተጨማሪ ቦታ ይለቅለታል፡፡

በዚህ ሳምንት ከተኛሽበት ወይም ከተቀመጥሽበት ወይም ጋደም ካልሽበት ቦታ ስትነሽ በእርጋታ  መሆን አለበት፡፡  ቶሎ ብድግ ብለሽ ከተነሳሽ ፈዘዝ እንደማለት ልትሆኚ ትቺያለሽ፤ ምክንያቱም ደም ወደ እግርሽ በመሄዱ ጭንቅላትሽ የደም ግፊቱ አነስተኛ ስለሚሆን ጭዉዉ ልትይ ትቺያለሽ፡፡ ማግሳትና አየር ወይም ፈስ እንዲሁም የሆድ ድርቀት ሊደጋገምብሽ ይችላል ፡፡  በተጨማሪም ማህፀንሽ ፈሳሾችን ሊያመነጭ ይችላል፡፡

በፊት እንደተጠቀሰዉ በየሳምንቱ ወደ ግማሽ ኪሎ ክብደት እየጨመርሽ ነዉ፡፡  የሆድሽን መጠን ብታስተዉይዉ አድጓል፡፡ የእግር ጥፍሮችሽን ማየት ከተሳነሽ ቆይቷል፡፡ከሆድሽ መክበድ ጋር ተያይዞ የጀርባ ህመም ይኖርሻል፡፡ ለረዥም ሰዓታት መቀመጥ የበለጠ ህመሙን ሊያጠናብሽ ይችላል፡፡ ሆድሽ በማደጉ የተነሳ ሳንባሽ እንደልቡ በሙሉ አቅሙ መለጠጥ ስለሚሳነዉ ትንሽ በተጓዝሽ ቁጥር የትንፋሽ ማጠር ያጋጥምሻል፡፡ የእግር ማበጥ የተለመደ ነዉ፣ እንዲሁም ጡቶችሽ መጠነኛ ፈሳሽ ማመንጨት ካልጀመሩ በዚህ ሳምንት ሊጀምሩ ይችላሉ፡፡ በእርግጥ አንዳንድ ሴቶች ጭራሹኑ ፈሳሽ ላያመነጩ ይችላል፡፡

በእርግዝና ወቅት ፀጉርሽ ያድጋል፤ባልጠበቅሽባቸዉ ቦታዎች ላይ ፀጉርሽ ያድጋል፣ ተንከባከቢዉ፡፡ ስትተኚ በግራ ጎንሽ ተጋደሚ፡፡

ከሀገር ሀገር ቢለያይም በዚህ ሳምንት ወይንም በሚቀጥለዉ ሳምንታት የስራ የወሊድ ፍቃድ ልትወስጂ ትቺያለሽ፤መልካም ዕድል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *