በ33ኛዉ ሳምንት

የመዉለጃሽ ጊዜ እየተቃረበ ነዉ፣ ሆድሽም ገፍቷል፤ በዚህም የተነሳ በምትንቀሳቀሺበት ጊዜ አንዳንድ ቁሳቁሶች ሆድሽን እንዳይገጩት መጠንቀቅ ይኖርብሻል፡፡

አጅሬ ልጅሽ ብርሃንና ጨለማን ከመለየቱም አልፎ ሲተኛ አይኖቹን ይጨፍናል ሲነሳም አይኖቹን ይከፍታል፡፡ በሆድሽ ዉስጥ አልፎ የሚመጣዉን ብርሃንና ጨለማ በደንብ ይለያል፤ልጅሽ ፀጉሩ ይኖረዋል፡፡በተጨማሪም ጭንቅላቱን ወደ ታች ዘቅዝቆ ማህፀንሽ ዉስጥ ተደላድሏል፡፡

በዚህ ጊዜ ፅንሱ አውራ ጣቱን መጥባት ይጀምራል።ቆዳው ትክክለኛውን መልክና ቀለም ይይዛል። የፅንሱ እንቅስቃሴ እና እርግጫ ከወትሮው ይጨምራል።

በአልትራሳዉንድ ፎቶ የልጅሽን ፈገግታ እና ሲስቅ እንዲሁም ሲያዛጋ ማየት ትችያለሽ ፡፡ ልጅሽ በማህፀንሽ ዉስጥ በማደጉ የተነሳ በሆድሽ ዉስጥ ያለዉ የአሚኖቲክ ፍሉድ ፈሳሽ ከወትሮዉ ባለፈ ቀነስ የሚልበት ወቅት ነዉ፡፡

በዚህ ሳምንት ዋና ብትዋኚ የበለጠ ያዝናናሻል፡፡ ዉሃዉ ክብደትሽን በመሸከሙ የሚሰማሽ የክብደት መቅለል ጥሩ ስሜት ይፈጥርልሻል፡፡ እንደተለመደዉ ቪታሚኖችን እንዲሁም የተመጣጠነ ምግብ መመገብ ይኖርብሻል፡፡

በዚህ ሳምንት በእንቅልፍ ጊዜ አስፈሪና አስጨናቂ ህልሞችና ቅዠቶች ሊያዩ ይችላሉ በዚህም የተነሳ የእንቅልፍ ችግር ሊያጋጥማቸዉ ይችላል፡፡ ይህም ችግር ከአራት እናቶች በሶስቱ ላይ ይከሰታል ተብሎ ይገመታል ፡፡ እንቅልፍ ኣጣሁ ብሎ መጨነቅ አስፈላጊ አይደለም፤ ይልቁንስ በተገኘዉ አጋጣሚ ሶፋ ላይ ጋደም በማለትየእንቅልፍ ችግሩን መፍታት ተገቢ ነዉ፡፡

የእንቅልፍ ማጣት ችግር ከበዛብሽ መፅሃፍ በማንበብና እራስን በማዝናናት ማሳለፉ አንድ አማራጭ ነዉ፡፡ከዚህና ከዚህ ቡኋላ የሚያጋጥምሽ የእንቅልፍ ማጣት ልጅሽ ከተወለደ ቡኋላ ለሚኖረዉ ጊዜ ምናልባት ጥሩ ልምድ ሊሆን ይችላል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *