ፅንሱ ወይም ልጅሽ ወደ 2.5 ሴንቲሜትር የሚያክል እርዝማኔ አለዉ፡፡ በዚህ ሳምንት ልቡ አድጎ የልብ ምቱንም በአልትራሳዉንድ ማየት ይቻላል፡፡ ፅንስሽም የሰዉ ቅርፅ መያዝ ይጀምራል፤ እግሮቹ እጆቹ ቦታ ቦታቸዉን መያዝ ይጀምራሉ ፡፡ አንገቱ ፣ጉበቱና ጣፊያዉ በማደግ ላይ ናቸዉ ፡፡ ዓይኑ ገና ባይስተካከልም የአይን ቦታዎች መፈጠር ጀምሯል፡፡ ትንንሽ ጡንቻዎችና የፆታ አካላቶቹ ቦታ ቦታቸዉን ይዟል፡፡
ልጅሽ መንቀሳቀስ ጀምሯል ነገር ግን እንቅስቃሴዉ አይሰማሽም፡፡
ሰዉነትሽ የእርግዝና ሆርሞኖችን እየለቀቀ ይገኛል፡፡ እነዚህ የእርግዝና ሆርሞኖች አንዳንድ ጊዜባንቺ ላይ የስሜት መለዋወጥ ይፈጥራሉ፡፡ ይህም መናደድ፣መጨነቅ፣በትንሽ ነገር መበሳጨት፣ መነጫነጭ ወይንም ከልክ በላይ ማሰብና የመሳሰሉት ነገሮች የእርግዝናዉ አካል ናቸዉ፡፡ ይህም በመሆኑ በተቻለ መጠን ሆርሞኖቹ እንደሆኑ በማሰብ እራስሽንለማረጋጋጽናስሜትሽን ለመቆጣጠር ሞክሪ፡፡
በዚህ ሳምንት ልብሶችሽ እየጠበቡሽ ይመጣሉ፤ በቀን በተደጋጋሚ ለትዉከትም ሆነ ለሽንት ወደ መፀዳጃ ቤት ልትመላለሽ ትቺያለሽ፡፡ ድካም የተለመደ ነዉ፡፡ የጭጓራ ቃጠሎና ቃር ካስቸገረሽ ቅመማቅመሞችና ቅባታማ የሆኑ ምግቦችን ለማስወገድ ሞክሪ፤ ያም ካልረዳሽ የጭጓራ መድሓኒቶች ወይንም ፀረ አሲድ (አንቲ አሲድ) የሆኑ መድሓኒቶችን ሀኪም ጋር በመመካከር መዉሰድ ትቺያለሽ፡፡
በተደጋጋሚ መሽናት ድካም እንዲሁም በዛ ያለ ምራቅ መትፋት ያጋጥምሻል፡፡ ጡቶችሽ ያድጋሉየጡትሽ ጫፍ ጠጥሮ የመጠዝጠዝ ስሜት ስላለዉ ማታ ማታ እንቅልፍ ሊነሳሽ ይችላል፤ ለዚህ አንዱ መፍትሄ ከጥጥ የተሰሩ ጡት ማስያዣዎች መጠቀም ወይም የእስፖርት ጡት ማስያዣዎችን ብትጠቀሚ ምቾት ሊሰጥሽ ይችላል፡፡
የሆድ ድረቀት ጋር ተያይዞ አንዳንድ እናቶች እንደ መፍትሄ የሚጠቀሙት ጡዋት ከእንቅልፍ ስትነሺ ለብ ያለ ዉኃከሎሚ ጋር አድርጎ መጠጣት ወይም ማታ ከመተኛትሽ በፊት ሳይበዛ ትንሽ ሞቅ ያለ ዉኃ ከሎሚ ጋር መጠጣት ለአንድ አንድ እናቶችየሆድ ድርቀቱን ይቀንሳል፡፡
በዚህ ሳመንት ለአለቃሽ ወይም ለስራ ቦታሽየእርግዝናሽንሁኔታ ምናልባት ማሳወቅ ሊኖርብሽ ይችላል፡፡ እንደ የማስሪያቤቱ እና እንደ ህጉ ወይንም እንዳንቺ የኑሮ ሁኔታ ቢወሰንም ከወዲሁ የወሊድ ፍቃድ ህግና ሁኔታዎችን ማወቅ ይጠቅምሻል፡፡
ባደጉ ሀገራት አሜሪካና አዉሮፓ ያሉ እናቶች በኢንተርኔት ወይም በፌስቡክ በመጠቀም ተመሳሳይ የእርግዝና ወቅት ያሉ እናቶች ግሩፕ አባል በመሆን ልምዳቸዉን ይጨዋወታሉ፡፡ ባለሽበት አካባቢ ወይንም ኢንተርኔት በመጠቀም ተመሳሳይ የእርግዝና ወቅት ካሉ እናቶች ጋር መገናኘት መልካም ነዉ ፡፡