እርግዝና ያለችግር እንዲሳካ(እንዲጠናቀቅ) ብዙ ነገሮች (ትክክለኛ የሆርሞኖች መጠን መኖር፣ ጤናማ የጽንስ ህዋስ መፈጠር እና ማደግ፣ የጽንስ ህዋስ በትክክለኛ ቦታ ላይ መቀበር፤ ወ.ዘ.ተ) ያስፈልጋሉ።
አንዳንዴ በዘር ህዋሶች መዳቀል የተፈጠረ የጽንስ ህዋስ በማህፀን ግርግዳ ላይ ሳይቀበር ከማህፀን አልፎ በሴቷ ብልት ሊወጣ ይችላል። ይህ ዘግየት ብሎ የተከሰተ የሚመስል የወር አበባ ዓይነት መድማት ሆኖ ይታያል። እናቲቱም ጽንሱ መፈጠሩን ላታስተውል ትችላለች።
በእኛ ሃገር ከ28 ሳምንት በፊት ፅንስ ከማህፀን ከወጣ እንደ ውርጃ ይቆጠራል። ከዚህ ጊዜ በኋላ የልብ ምት ሳይኖረው የሚወለድ ፅንስ ያለህይወት የተወለደ ፅንስ (still birth) ይባላል።
ውርጃ ሲከሰት የተለያዩ ደረጃዎች አሉት። በማህፀኑ ውስጥ ያለው የፅንሱ ይዘት በሙሉ ከማህፀን አልፎ ወጥቶ የማህፀን በር መልሶ ሲዘጋ የተጠናቀቀ ውርጃ (complete abortion) ይባላል። የተወሰነው የማህፀኑ ይዘት ብቻ ወጥቶ የተወሰነው ደግሞ በማህፀን ውስጥ ሲቀርና የማህፀን በር ክፍት ሆኖ ደም መፍሰስ በሚያስከስትበት ጊዜ ከፊል ውርጃ (incomplete abortion) ይባላል። በዚህ ሁኔታ የደም መፍሰሱ እንዲቆም ተጨማሪ መድሃኒቶች ወይም በመሳሪያ የማህፀኑን በር የበለጠ በመክፈት የቀረውን ይዘት ማውጣት አስፈላጊ ነው።
አንዳንድ ጊዜ ማህፀን ውስጥ ያለው ፅንስ ህይወት ሳይኖረው የተወሰነ ደም ብቻ ፈሶ የማህፀን በሩ እንደተዘጋ ሊቆይ ይችላል። ይህም ሁኔታ የቀረ ውርጃ (missed abortion) ይባላል። ህክምናውም በመድሃኒት ወይም በመሳሪያ የማህፀን በሩን በመክፈት የማህፀኑን ይዘት ማውጣት ነው።
በሃገራችን አንዲት ነፍሰ ጡር በተለያዩ ምክንያቶች ህጋዊ በሆነ ሁኔታ እርግዝናዋን በህክምና እንድታቋርጥ (እንድታስወርድ) ይፈቀዳል።
እነዚህም ሁኔታዎች፡
- እርግዝናው በእናቲቱ ህይወት ላይ ከፍተኛ የህክምና አደጋ የሚያመጣ ከሆነ፣
- ፅንሱ ከተወለደ በኋላ በህይወት ሊኖር የማያስችለው ችግር ወይም ከፍተኛ የሆነ የአካል ወይም የአእምሮ ጉዳት እንዳለው ከታወቀ
- እናቲቱ የፀነሰችው በማስገደድ ተደፍራ ከሆነ
- እናቲቱ የፀነሰችው የቤተሰብ አባል ከሆነ ሰው ከሆነ
- እናቲቱ ብትወልድ ከወለደች በኋላ ልጁን ለማሳደግ የማያስችላት የሰውነት፣ የአእምሮ ችግር ያለባት እንደሆነ ናቸው።
ይህን ህጋዊ ሁኔታ የሚያሟላ እርግዝና ያላት ነፍሰ ጡር በማንኛውም አገልግሎቱን በሚሰጥ ተቋም በፈቃዷ ንፁህ በሆነ ሁኔታ ፅንሷን ልታስወርድ ትችላለች።