አንዳንድ ሴቶች ልጅ እንዲኖራቸው ቢፈልጉም ወይ ደጋግሞ ይጨናገፍባቸዋል ወይንም ደግሞ ቅሪት መያዝ አይችሉም:: ይህ ሲሆን Infertility መካንነት ወይም መሃንነት ይባላል፤ ሀሳቡ ጊዜያዊ ማርገዝ ያለመቻልን ለማመላከት ሆኖ ነገር ግን በህክምና እስካልተረጋገጠ ድረስ እራስን እንደ መሀን ማሰብ የለብንም:: ከአመት ሙከራ በኋላ ወይም ከ35 አመት በላይ ለሆነች ሴት ደግሞ ከ 6 ወር በኋላ ቅሪት ካልያዘች ለበለጠ እርዳታ ወደ ዶክተር መሄድ ይመከራል:: የመካንነት ችግር በሴቶችም ላይ ሆነ በወንዶች ላይ የሚከሰት ነው:: ዶክተሮች መውለድ ያልቻሉ ጥንዶችን መውለድ እንዲችሉ ሊረዱ ችለዋል::
በቀጥታ ነፍሰጡር ባለመሆናችሁም ልትገረሙም ሆነ ልትበሳጩ አይገባችሁም:: በአብዛኛው የሚዘገይ ነው፣ ይህም የተለመደ ኖርማል ነው:: አስታውሱ ከ100 ጥንዶች ከ 80-90 የሚሆኑት በመጀመሪያው አመት ነፍሰጡር ይሆናሉ:: ከ100 ጥንዶች 95 የሚሆኑት ደግሞ በ ሁለት አመት ውስጥ ነፍሰጡር ይሆናሉ:: በአንዴው ነፍሰጡር አልሆንሽም ማለት ችግር አለ ወይም ደግሞ ከተለመደው የወጣ ነው ማለት አይደለም:: ከወራት ሙከራ በኋላ እንኳ ነፍሰጡር አለመሆን ሊያስጨንቅ አይገባም – የተለመደ ኖርማል ነው::