የተፈጥሮ ወሊድ ለህጻኑም ሆነ ለእናቲት ከ ሲ-ሴክሽን (ቀዶ ጥገና) ወሊድ በጣም ደህንነት ያለው ነው። አንዳንድ ጊዜ ለምሳሌ የህጻኑ አቀማመጥ በሆድ ውስጥ ወደጎንና ወደጎን ከሆነ ወይም የእንግዴ ልጁ ሰርቪክስን (የማህፀን በርን ወይም ህፅንተ አንገትን) (የእንግዴልጅ ፕሪቪያ) ከሸፈነ፤ የ ሲ-ሴክሽን ወሊድ ብቸኛ አማራጭ ይሆናል። በአንዳንድ ሁኔታዎች ሲ-ሴክሽን የተወሰነ ጥቅም ይኖረዋል፤ ጉዳቱና ጥቅሙን ማመዛዘን ያስፈልጋል:: ጥቅሙንም ሆነ ጉዳቱን ከህክምና ባለሙያዎች በመረዳት፤ የሚጠቅመውን መወሰን የጥንዶቹ መብት ነው።
ጥቅሙ መሰረት የሚያደርገው በእርግዝናና በምጥ ወቅት ባለው ሂደት ይሆናል:: የህክምና ባለሙያው ወይም አዋላጇ ምጥ ወይም ተፈጥሯዊ ወሊድ ለህጻኑም ሆነ ለእናት አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል ካሰቡ የሲ-ሴክሽን ወሊድ ይመክራሉ።
ለምሳሌ፣ በቂጡ በኩል የዞረን ህጻን ለመውለድ አስቸጋሪ ይሆናል፣ በዚህ አይነት አቀማመጥ ያሉትን በተፈጥሯዊ ወሊድ ለማድረግ መሞከር ህጻኑን ሊጎዳ ይችላል። ወይም በምጥ ጊዜ የጽንሱ የልብ ምት ለውጥ ካሳየ፣ ህጻኑ በቂ ኦክስጅን እያገኘ አለመሆኑን ያመለክታል:: በእነዚህ የተለዩ ሁኔታዎች፣ የሲ-ሴክሽን ወሊድ ህጻኑ የመጎዳቱን እድል ይቀንሰዋል።
ምንም እንኳ ምጥ እና ተፈጥሯዊ ወሊድ ከባድ ስራ ቢሆንም፣ ከቀዶ ጥገና ወሊድ ሲነጻጸር በጥቅሉ ለሴቶች አካል ቀለል ያለ ነው። ከሲ-ሴክሽን ወሊድ በተለየ ተፈጥሯዊ ወሊድ በተለምዶ የማገገም ሂደቱ አጭር እና ያነሰ ህመም ያለው ነው፤ እንዲሁም ሴቶች ከልጆቻቸው ጋር ይበልጥ ጊዜ እንዲኖራቸው ያደርጋል። አዳዲስ ጥናቶች እንደሚያመለክቱትም ምጥ እና ተፈጥሯዊ ወሊድ ለህጻናቱም ጥሩ ናቸው።
ምጥን እንዲጀምር የሚያደርገውና የሚያስቀጥለው ሆርሞንም ልጁ ለመወለድ ዝግጁ እንዲሆን ይረዳል፣ አንዳንድ የመተንፈሻ አካል ችግሮችንም ይቀንሳል። በተፈጥሮ የሚወለዱ ህጻናትም ከባድ ከሚባሉት የህጻናት በሽታዎች እንደእነ አስም፣ ስኳርና አላርጂክ የመያዝ እድላቸው አናሳ ነው፤ ለተጋነነ ውፍረትም አይጋለጡም። አጥኚወች እንደሚያስቡትም ይህን ጥቅም የሚያገኙት በወሊድ ጊዜ ለጤናማ ባክቴሪያወች ስለሚጋለጡ እንደሆነ ነው።
ሲ-ሴክሽን የቀዶ ጥገና ወሊድ ነው:: ሁሉም ቀዶ ጥገናዎችም የራሳቸው የሆነ አደጋ አላቸው፤ ልክ እንደ ኢንፌክሽን፣ የሰውነት ክፍሎች እና የደም ቱቦዎች ላይ የሚደርስ ቁስልና የደም መፍሰስ። ሲ-ሴክሽን በህጻናት ላይም ችግር ያመጣል፣ እንደ መተንፈሻ አካል ችግሮች ስለዚህም በጨቅላ ህጻናት ክትትል ክፍል ወይም ኢንተንሲቭ ኬር ዩኒት ህክምና ያስፈልጋቸዋል። ከሲ-ሴክሽን በኋላ ያለ የማገገም ሂደትም ከተፈጥራዊ ወሊድ አንጻር አስቸጋሪ ነው። ለበለጠ መረጃ የህክምና ባለሙያዎን ያማክሩ።