የእርግዝና ክብደት፡ – በአማካይ አብዛኞቹ ሴቶች በመውለጃቸው በመጨረሻው ሳምንት ከ10 ኪሎ እስከ 12.5 ኪሎ ተጨማሪ የሰውነት ክብደት በእርግዝናው የተነሳ ያካብታሉ፡፡ ከዚህ ክብደት ውስጥ ደግሞ በአማካይ ወደ 5 ኪሎ የሚገመት ክብደት በወሊድ ወቅት ከሰውነት ይቀነሳል፡፡ በመጨረሻም ከወሊድ በኋላ በእርግዝናው የተነሳ ከ 5 ኪሎ እስከ 7.5 ኪሎ በቀድሞው ክብደት ላይ ተጨማሪ የሰውነት ክብደት ይኖራል፡፡
ከወሊድ በኋላ ከ6 እስከ 12 ወራት ባለው ጊዜ ውስጥ ከእርግዝና በፊት ወደነበራችሁበት ክብደት ለመመለስ ትችላላችሁ:: ለዚህ ማቀድና ዕቅዱን በፅናት መከታተል ያስፈልጋል፡፡ በመጀመሪያው ስድስት ሳምንት ሰውነታችሁ ከምጥ እና ከወሊድ በኋላ እንዲያገግም በቂ ጊዜ ነው:: አብዛኞቹ ሴቶች የእርግዝና ክብደታቸውን ግማሽ ያህሉን ከወሊድ በኋላ ባለው 6 ሳምንት ውስጥ ይቀንሳሉ:: ቀሪውን በተከታዮች ወራት ሂደት በሂደት ይቀንሱታል::
ጡት ማጥባት ሰውነታችሁ ካሎሪ እንዲያቃጥል ይረዳችኋል:: ክብደት እንድትቀንሱ ይረዳችኋል:: ትግስተኛ ከሆናችሁ፣ ጡት በማጥባታችሁ ብቻ በተፈጥሮ የምትቀንሱት ክብደት የሚያስገርም ነው::