የህጻን ማልቀስ

በመጀመሪያወቹ ወራቶች የጨቅላው ብቸኛ ፍላጎቱን ማሟያ የመግባቢያ መንገድ የሚሆነው ማልቀስ ነው:: ማልቀሱ ጨቅላው መሽናቱን፣ መድከሙን፣ መራቡን፣ ብቸኝነትን፣ እንዳልተመቸው፣ እንደተጸዳዳ፣ እንቅልፍ እንደፈለገ፣ መታቀፍ እንደፈለገ፣ ሆዱን እንዳመመው(ፈስ፣ ላክቶስ ኢንቶለራንስ፣ መጸዳዳት አለመቻል፣ የአንጀት መዘጋት እና ሌሎችም)፣ ማግሳት እንደፈለገ፣ እንደበረደው ወይም እንደሞቀው፣ የሆነ ትንሽ ነገር እየቆረቆረው እንደሆነ፣ ደህና ስሜት እንዳልተሰማው ወይም ደግሞ ጉሮሮውን እያለማመደ መሆኑንን የሚያመላክት ነው::

የጨቅላው ድርጊቶች እና ማልቀሱ ምን ማለት እንደሆነ ለመረዳት ጊዜ  ይወስዳል፡፡ ይህ ለአንዳንዶች አስቸጋሪ ሂደት ነው:: እንደማንኛውም የህይወት ሁነቶች፣ እነዚህን ነገሮች በሂደት መማር ያስፈልገናል፤ ወይ በሙከራ እና በስህተት፣ ወይም በማንበብ ና በመጠየቅ፣ ወይም ከባለሙያ ጋር አብሮ በመዋል:: በሂደትም ስለ ጨቅላው ባህርይ ይበልጥ የሚረዱት ይሆናል፡፡