እርግዝናና ምግብ

ጤነኛ የአመጋገብ ዘይቤና የአኗኗር ዘይቤ በእርግዝና ወቅት እራስሽን ለመጠበቅና ለልጅሽ ጥሩ የህይወት ጅምር ለመስጠት እንድትችይ ይረዳሻል። በእርግዝና ወቅት ልጅሽ ኃይልና ንጥረ ነገሮችን የሚያገኘው ካንቺ ነው። ስለዚህ የተመጣጠነ ምግብ መውሰድ ይኖርብሻል።
ምን መመገብ አለብሽ?
ጤነኛ አመጋገብ አርግዘሽ ከሆነ ወይም ለማርገዝ እያሰብሽ ከሆነ በጣም አስፈላጊ ነው። በእርግዝና ወቅት ጤነኛ አመጋገብ ፅንሱ እንዲያድግና አንቺም ጤነኛና ጥሩ አቋም እንዲኖርሽ ይረዳሻል። ልዩ የሆነ የአመጋገብ ዘይቤ መከተል የለብሽም፣ ነገር ግን ለአንቺና ለልጅሽ የሚያስፈልገውን የተመጣጠነ ምግብ በየቀኑ ማግኘት አለብሽ።

ከሌላው ጊዜ በበለጠ የርሃብ ስሜት ሊሰማሽ ይችላል፣ ነገር ግን መንታ ብታረግዢም እንኳን ለሁለት ሰው መመገብ የለብሽም። በየቀኑ በተቻለ መጠን ቁርስ፣ ምሳ፣ እራት እና በመሃል ጤናማ መቆያ ምግብ(መክሰስ) መብላት አለብሽ፣ ይህን ማድረግሽ ብዙ ስብ እና ስኳር የበዛበት መቆያ ምግብ ከመመገብ ይጠብቅሻል። ሁሉንም የምትወጃቸውን ምግቦች ከመተው ይልቅ መጠናቸውን መቀነስ ትችያለሽ።

ጤናማ ፅንስና የተመጣጠነ ምግብ

ለጤናማ እርግዝና እና ጤናማ ፅንስ የተመጣጠነ ምግብ መመገብ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው። የተመጣጠኑ ምግብ ዓይነቶች ሊገኙ የሚችሉት ፡-

  • ፕሮቲን (ሰውነት ገንቢ): ስጋ፣ ዓሳ፣ እንቁላል፣ የወተት ውጤቶች የመሳሰሉት፡፡
  • ቅባት :- ቅቤ፣ ዘይት፣ ማርጋሪን/የዳቦ ቅባት/፣ የወተት ውጤቶች፡፡
  • ኃይልና ሙቀት ሰጪ ፡-ዳቦ፣ፓሰታ፣ ድንች፣ ሩዝ፣ በቆሎ፣የአዝዕርት ውጤቶችና የመሳሰሉት፡፡
  • ቫይታሚኖች ፍራፍሬ፣ አትክልቶች፣ ፎሊክ አሲድ/ቫይታሚን ቢ9 በመጀመሪያዎቹ ሶስት የእርግዝና ወራት ከጥራጥሬዎች፣ ፍራፍሬዎች፣ ብርትኳን ጭማቂ፣ ሩዝ እና ከመሳሰሉት ማግኘት ይቻላል፡፡